ፈረንሳይ በፕሬዝደንታዊ ምርጫ ላይ ተገኛለች



በአውሮፓ ህብረት ውስጥ ካሉ ግዙፍ ኢኮኖሚዎች አንዱ፣የአውሮፓ ህብረት መስራች፣የአውሮፓ ፖለቲካ ማዕከላዊ ተዋናይ የቀጠናውን ኢኮኖሚ በከፍተኛ ደረጃ ተፅእኖ የምታደርገው ሀገር ፈረንሳይ፡፡በፕሬዝደንታዊ ምርጫ ላይ ተገኛለች፡፡የፈረንሳይ ኢኮኖሚ የአውሮፓ ህብረትን አጠቃላይ ኢኮኖሚ 15 ፐርሰንት ይሸፍናል፡፡በፖለቲካዊ ውሳኔዎችም ረገድ ፈረንሳይ በአውሮፓ ህብረት ወሳኝ ከሆኑት መካከል ነች፡፡በአውሮፓ ህብረት ፓርላማ ውስጥ ከሚገኙት 751 ወንበሮች ፈረንሳይ 74 ይዛለች፡፡ይህም አስር ፐርሰነት ያክል የድምፅ ውሳኔን የሚሸፍን ነው፡፡በአውሮፓ ህብረት የሚኒስተሮች ምክርቤት ደግሞ ከ352 መቀመጫዎች ውስጥ 29 በፈረንሳይ የተያዘ ነው
በቅርብ አመታት ውስጥ የአውሮፓ ህብረት መገበያያ ገንዘብ የሆነው ዩሮ ከዶላር ጋር ያለው የምንዛሬ አቅም እየቀነሰ መጥቷል፡፡ አውሮፓ 500 ሚሊየን ሸማቾች ያሉት ግዙፍ ገበያ ቢሆንም በተለያዩ ፖሊቲካዊና የህብረቱ ሀገራት ውስጣዊ ኢኮኖሚ መዳከም ምክንያት የሚፈለገውን ያክል መንቀሳቀስ አልቻለም፡፡በግሪክ የተከሰተው የፋይናንስ ቀውስ የአውሮፓ ሀገራትን ኢኮኖሚ ድምር እድገት ቀንሶታል፡፡ከአፍሪካና ከሩቅ ምስራቅ የሚመጡ ስደተኞችም የህብረቱ የአኮኖሚም ሆነ ፖለቲካ ፈተናዎች ሆነዋል፡፡በሌላ በኩል ሽብረተኞች በቀጠናው በሚያደርሱት አደጋ ምክንያት ወደ አከባቢው ይገባሉ ተብለው የሚጠበቁ ግዙፍ አምራች ደርጅቶችና ኢንቨስተሮች ወደ አውሮፓ የመምጣታቸውን ጉዳይ በእጅጉ ቀንሶታል፡፡እነዚህ ጉዳዮች ተደማምረው የህበረቱን የመቀጠል ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ እየከተቱት ነው፡፡በተሌም እንግሊዝ ከህብረቱ የመውጣቷ ጉዳይ ሌሎችም ይከተላሉ የሚለውን ስጋት የፈጠረ ነው፡፡



 

በፈረንሳይ በስልጣን ላይ የሚገኘው የሶሻሊስት ፓርቲም ኢኮኖሚውን በማስተዳደሩ በኩል በስልጣን በነበረባቸው ዓመታት ያሳየው አፈፃፀም ደካማ ነበር እየተባለ ነው፡፡የሶሻሊስት ፓርቲውን ወክለው ወደ ፕሬዝደንትነቱ የመጡት ፍረንሷ ሆልንዴ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ የፈርንሳይ ኢኮኖሚ እድገት ከ1 ፐርሰነት በታች ሆኖ ነው የቆየው፡፡የስራ አጥነት ቁጥሩም ከ10 ፐርሰንት በላይ ደርሷል፡፡ይህም በጀርመንና በእንግሊዝ ካለው የ4 ፐርሰነት የስራ አጥነት ደረጃ ጋር ሲነፃፀር እጅግ ከፍተኛ የሚባልለት ነው፡፡የዩሮም ከዶላር ጋር ያለው የውጭ ምንዛሬ ደረጃ ወደ አቻ እየመጣ ነው፡፡

በፈረንሳይ እየተካሄደ ባለው ምርጫም ዋነኛው ጉዳይ ይህን ከፍተኛ የስራ አጥነት ቁጥር መቀነስና ከሌሎች የአውሮፓ ሀገራት ጋር ያለውን ግንኙነት ምን መምሰል አለበት እስከሚለው የሚደርስ ነው፡፡ለሀገሪቱ የማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊ፣የስደተኞች ጉዳይ፣ኢንዱስትሪና የመከላከያ ጉዳዮች ከፍተኛ ትኩረትም ተሰጥቷቸዋል፡፡የአሁኑ የፈረንሳይ ፕሬዝድነት ፍራንሷ ሆላንዴ ዳግም በምርጫ በማይሰተፉበት ምርጫ ብዙ ቁጥር ያላቸው እጩዎች ወደ ፕሬዝደንታዊው ፍልሚያ ገብተው አሁን ላይ ሁለት እጩዎች ብቻ ቀርተዋል፡፡ማሪን ሌፔን እና  ኢማኑኤል ማክሮን፡፡የናሽናል ፈሮንት ፓረቲ መስራች የሆኑት ዢያን ማሬ ሌፔን ልጅ የሆኑት ማሪን ሌፔን በፕሬዝድንታዊው ፉክክር በከፍተኛ ደረጃ በህዝብ ተቀባይነት ያገኙ ናቸው፡፡የመንግስት ጠንካራ የአኮኖሚ ውስጥ ጣለቃ ገብነት፣የድንበር ላይ ጥበቃ፣የፈረንሳይ መገበያያ ገንዘብ ፍራንክ ከዩሮ ጋር ጎን ለጎን እንዲሰራ ማድረግ እጩ ፕሬዝደንታዊ ተወዳዳሪዋ ማሬን ሌፔን ለምርጫ ወድድር ያቀረቧቸው ማሻሻያዎች ናቸው፡፡በዚህም ሀሳባቸው በግብር በከፍተኛ ሁኔታ የተጎዳውና በስራ አጥነት በተሰቃየው የፈርንሳይ  ሰራተኛ  ህዝብ በኩል ከፍተኛ ድጋፍን አግኝተዋል፡፡
በአሁኑ የፈርንሳይ ፕሬዝድንት ፍራንሷ ሆላንዴ አስተዳደር የፋናንስ ሚኒስቴር ኢማኑኤል ማክሮን የሌፔን ተፎካካሪ ፕሬዝደንታዊ እጪ ናቸው፡፡በሳምንት 35 የስራ ሰዓት፣የጡረታ ጊዜ እንደሁኔታው ሊለዋወጥ የሚችል መሆኑና ለአውሮፓ ህብረት መጠናከር ፈረንሳይ የበጀት ዝውወር ወደ ሌሎች የህብረቱ ሀገራት ማድረግ አለባት ለዚህ እሰራለሁ የሚል ሀሳብ ይዘው በፍልሚያ ውስጥ ገብተዋል፡፡
ፈረንሳይ ታማኝ የአውሮፓ ህብረት ደጋፊና ህብረቱ በ1950 ሲጠነሰስ መስራቻ ከሆኑት ሀገራት መካከል አንዷ ናት፡፡ስለዚህም ፕሬዝደንታዊ ዕጩዎቹ እንደ እንግሊዝ ከአውሮፓ ህብረት የመውጣት አማራጭን ይፍጥራሉ ተብሎ አይገመትም፡፡ነገር ግን የእንግሊዘ ከአውሮፓ ህብረት መውጣት፣የአሁኑ የፈረንሳይ ፕሬዝድንትና የአውሮፓ ህብረት ፅኑ ደጋፊ ፍራንሷ ሆላንዴ በፕሬዝድነታዊ ምርጫው አለመሳተፋቸው፣ሌላው የህብረቱ ደጋፊ የሆኑት የጣልያኑ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስቴር በህዝበ ውሳኔ ተሸንፈው ከስልጣናቸው በገዛ ፍቃዳቸው መልቀቃቸው የጀርምኗን ቻንስለር አንጌላ መርክልን በቀጠናው ብቸኛው አውሮፓ ህብረት መኖርን የሚደግፉ ያደርጋቸዋል፡፡
በአሜሪካን የትራምፕ ወደ ፕሬዝድንትነቱ መምጣት እና ባሰለፏቸው አንድ መቶ ቀኖች የወሰዷቸው የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎች እንዲሁም የሩሲያው ፕሬዝድነት በቀጣናው የአውሮፓ ህብረት ሀገራት ላይ እየወሰዱ ያሏቸው እርምጃዎች ለፈረንሳይም ሆነ ለህብረቱ ሀገራት ጫኑ የፈጠሩ ናቸው፡፡ይህም ሁኔታ ፈረንሳይና ሌሎች ተፅዕኖ ፈጣሪ የህብረቱ አባላት ከአሜሪካንና ከሩሲያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ዳግም እንዲያጤኑ አስገድዷቸዋል፡፡እስከ አሁኗ ሰዓት ድረስ ግን ሁሉም የህብረቱ ሀገራት ሩስያ የቀድሞ የዩክሬን ግዛት የሆነችው ክሬሜያን ወደራሷ ግዛት ማስገባቷና በሶርያ ግጭት ውስጥ በሻር አላሳድን በከፍተኛ ደረጃ የመደገፏ ጉዳይ ላይ ምን ማድረግ እንደሚገባቸው ከስምምነት ላይ አልደረሱም፡፡ይብሱን ልዩነታቸው እየሰፋ መጥቷል፡፡በዚህ ልዩነት ውስጥ ሆነው ግን በሩሲያ ላይ ዋነኞቹ ግዙፍ ኢኮኖሚዎች የአኮኖሚ ማዕቀብ መጣላቸው አልቀረም፡፡ሩሲያም በበኩሏ በአውሮፓ ህብረት ምርቶች ላይ የራስዋን ማዕቀብ ጥላለች፡፡ሩሲያ ክሬሚያን በሃይል ወደ ራሷ ግዛትነት ከወሰደች በኋላ በሩሲያ ላይ በተጣለው ማዕቀብ ምክንያት አውሮፓና ሩሲያ በድምሩ 100 ቢሊየን ዶላር አጥተዋል፡፡ለምርጫ ተወዳዳሪዎቹም ትልቁ ፈተና ከሩሲያ ጋር የሚኖረው ግንኙነት ሲሆን ይህ በሩሲያ ላይ የተጣለውን ማዕቀብም ማላላትን ይጨመራል፡፡

 
የፈረንሳይ የውጪ ቀጥተኛ ኢንቬስትመንት ከ2012-2017 ባሉት ተከታታይ ዓመታት በከፍተኛ ደረጃ ቀንሷል፡፡በተለይም በህዳር ወር በፓሪስ ከደረሰው የሽብረተኝነት ጥቃት ጋር በተያያዘ የውጪ ኢንቨስተሮች አይናቸውን ከህብረቱም ሆነ ከፈረንሳይ ዞር ያደረጉ ይመስላሉ ይህም በኢኮኖሚው ላይ በፈጠረው መቀዛቀዝ ከፍተኛ የሚባል ነው፡፡
የፈረንሳይ ፕሬዝደንታዊ ምርጫን ተከትሎ በዩሮ ቀጣና ከፍተኛ ለውጥ ይጠበቃል፡፡የአውሮፓ ህብረት መገበያያ ገንዘብ ዩሮን ማጠናከር አልያም ደግሞ ጎን ጎን ለጎን የፈረንሳይ መገበያያ ገንዘብ ፍራንከን ማስተዋወቅ፣የፈረንሳይን ድንበር በማጠናከርና ለፈረንሳይ ዜጎች ሰፊ የስራ እድለ በመፍጠር መንቀሳቀስ አልያም ደግሞ በአውሮፓ ህብረት ውስጥ ጠንካራ ግንኙነት በመፍጠር የቀደመውን አካሄድ ማስቀጠል የሚሉት ጉዳዮች በሁለቱ የምርጫ ተወዳደሪዎች ማካከል ያፈጠጡ እውነታዎችና በምርጫው ውሳኔን የሚያገኙ ናቸው፡፡
ፈረንሳውያን ወደ መጨረሻው የምርጫ ሂድት ውስጥ ሲገቡ የሀገሪቱ ከአውሮፓ ህብረት ጋር የሚኖራት ግንኙነት፣ቀጠናውን እያመሰ ያለው የስደተኞች ጉዳይና ሽብርተኝነት ወሳኞቹ የመምረጫ መስፈርቶቻው ይሆናሉ፡፡በፈረንሳይ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ተመርጦ  ወደ ኤሊስ ፓላስ የሚገባው ማንም ይሁን ማንም ቀጣዩ ጊዜ ለአውሮፓ ህብረትም ሆነ ለፈረንሳይ ፈታኝነቱ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡

Comments

Popular Posts